ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎች መምህራኖቻቸውን እና ወላጆቻቸውን የማመስገን እና የማድነቅ ሀገር አቀፍ መርሀ-ግብር አካሂዷል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ መምህራኖች፣ ወላጆች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ፒ ኤች ዲ) ወላጆችን እና መምህራኖችን ማመስገን እና ማድነቅ ለከፈሉት መሰዎትነት እና ላመጡት ውጤት እውቅና መስጠት ነው ብለዋል።
በቀጣይ አመት ወደ ተግባር በሚገባው አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ውስጥም የግብረ ገብ ትምህርት ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን እና በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር እንደሚሰራ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
ወላጆች ፣ መምህራኖች እና ማህበረሰቡ በስነምግባር የታነፀ ትውልድን ለመፍጠር ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራ የመመሰጋገን መርሀ ግብሩ የሚያመሰግን ትውልድ እንዲፈጠር የማድረግ ፋይዳ አለው ብለዋል።
መምህራን ትውልድን በመቅረፅ ከፍተኛ አስተዋጾ የሚያበረክቱ አካላት መሆናቸውን እና መምህርነት ትውልድን የምናነቃበት ሙያ በመሆኑ ተገቢውን ምስጋና መስጠት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
ወላጆች የነገ ትወልድን ከማፍራት አንፃር ላበረከቱት አስተዋጾ ማመስገንም እንደሚገባ ተናግረዋል።
የቅን ኢትዬጵያ የቦርድ ሰብሳቢ መሰለ ሀይሌ(ፒ ኤች ዲ) መከባበር እና መደናነቅን በማስፋት መልካም ትውልድን ማፍራት እንደሚገባ ገልፀዋል።
ተማሪዎችም በመምህራን እና ወላጆች የሚደረግላቸውን ድጋፍ በአግባቡ በመጠቀም ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ እናምሳሌ እንዲሆኑ ተገልጿል።
በመድረኩሞ ተማሪዎች ለወላጆቻቸው እና ለመምህራኖቻቸው ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል።
የምስጋና መርሀ ግብሩም በየአመቱ ግንቦት በገባ የመጀመሪያው ሳምንት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚከበርም ተገልጿል።
ፕሮግራሙን ትምህርት ሚኒስቴር ከቅን ኢትዬጵያ ጋር በጋራ በመሆን ያዘጋጀው ነው።
Via MoE