በሀገር አቀፍ ደረጃ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ የብቃት መመዘኛ ፈተና ለመውሰድ እስከ አሁን 311 ሺህ 421 ተማሪዎች መመዝገባቸውን የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ።
በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦንላይን ለሚደረገው የ12ኛ ክፍል ሃገር አቀፍ ፈተና 500 ሺ ታብሌቶች ተዘጋጅተዋል።
በሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የተፈታኞች ምዝገባና ውጤት ጥንቅር ዳይሬክተር አቶ ዩሴፍ አበራ እንደገለጹት፤ የአጠቃላይ ሀገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ብቃት መመዘኛ ፈተና ከጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ ለመስጠት መርሐግብር ተይዟል።
በዚህ መሰረት የተማሪዎች ምዝገባ መደረጉን ገልጸው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ብቃት መመዘኛ ፈተና ለመውሰድ እስከ አሁን 311 ሺህ 421 ተማሪዎች መመዝገባቸውን አስታውቀዋል።
ምዝገባው ከትግራይ ክልል እና ከቤንሻንጉል ጉምዝ መተከል ዞን በስተቀር በሁሉ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካሄዱን ገልፀዋል።
በትግራይ ክልልና በመተከል ዞን ካጋጠመው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ተማሪዎችን ለመመዝገብ እንዳልተቻለ አመልክተዋል።
በትግራይ ክልልና በመተከል ዞን ቀደም ሲል ምዝገባ የተጀምረ ቢሆንም ከጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ መቋረጡን አስታውሰው፤ በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎችን ለመመዝገብ የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል።
በትግራይ ክልል 80 ያህል ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በመተከል ደግሞ እስከ 14 ትምህርት ቤቶች አሉ ተብሎ ይገመታል፣ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች ምዝገባ ከተደረገ ቁጥሩ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።