ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 2 በወረቀት በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች በቂ የስነልቦና ዝግጅት እንዲኖራቸው በሚደረገው ጥረት ወላጆች እና ማህበረሰቡ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ ጥሪ አቀረበ፡፡
በጋምቤላ ክልል ሀገር አቀፍ ብሄራዊ ፈተናውን በመደበኛ፣ በግል እና በማታ 3653 ያህል ተማሪዎች ይወስዳሉ።
ለፈተናው 17 የፈተና ጣቢያዎች ዝግጁ መሆናቸውን ተገልጿል።
ፈተናውን ለመስጠት ልዩ ልዩ የፈተና ቁሳቁሶች ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን የፈተና ሂደቱን ሊያስተባብሩ የሚችሉ አካላትን የመምረጥ ስራ እንደሚከናወን ክልል አሳውቋል።
የዘገየው የ8ኛ ክፍል ውጤት ጉዳይ ፦
የጋምቤላ ክልል አቀፍ የ8ኛ ክፍል ፈተና ውጤት በሚቀጥሉት ሁለት (2) ሳምንታት ለተማሪዎች ይፋ እንደሚደረግም የክልሉ ትምህርት ቢሮ አመልክቷል፡፡
ቢሮው ለስምንተኛ ክፍል ፈተና ውጤት መዘግየት እርማቱን ለማከናወን ባለሙያዎችን በበቂ ሁኔታ አለማግኘት በምክንያትነት አስቀምጧል።
ከአሁን በፊት ክልላዊ ፈተናው በክረምት ሰዓት ይታረም ስለነበር በወቅቱ ደግሞ በርካታ መምህራንን ማሳተፍ ይቻል እንደነበር የተገለፀ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በ60 መምህራን ብቻ እንዲታረም መደረጉ እንዲዘገይ አድርጎታል ተብሏል።
በቀጣዮቹ 2 ሳምንታት የ8ኛ ክፍል የተማሪዎች ውጤት ይፋ እየተሰራ እንደሚገኝ ቢሮው ያሳወቀ ሲሆን ተማሪና የተማሪ ቤተሰቦች ውጤቱን በትዕግስት እንዲጠባበቁ ጥሪ ቀርቧል።
የጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬተሪያት
የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ
አቶ ሙሴ ጋጂት (የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ)