በዲላ ከተማ የሚኖር ታዳጊ የቀዶ ህክምና በተደረገለት ማግስት በሆስፒታል አልጋው ላይ ሆኖ የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ወስዷል።
ታዳጊው በዲላ ከተማ ታህሳስ 6 ቀን 2013ዓ.ም. ምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ አንድ ቦታ ደርሰን እንመጣለን ብሎ ከቤት ይዞት የወጣው የእንጀራ አባቱ በስለት ወግቶ ጉዳት ያደርስበታል።
በማግስቱ የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ለመቀበል በዝግጅት ላይ የነበረው ታዳጊ አዲሱ ገብረሚካኤል በወቅቱ ባሰማው የይድረሱልኝ ጩኸት በአካባቢው የነበረ አንድ የመከላከያ ሠራዊት አባል ሆስፒታል ያደርሰዋል።
"ለፈተናው ስዓታት በቀሩበት ማግስት በተፈጸመብኝ ጥቃት ድንጋጤ ውስጥ ብገባም ቀደም ብዬ በቂ ዝግጅት በማድረጌ በሆስፒታል አልጋዬ ላይ ሆኜ ለመፈተን ባቀረብኩት ጥያቄ ተፈቅዶልኝ ተፈትኛለሁ በዚህም ጥሩ ውጤት እንደማመጣ እርግጠኛ ነኝ" ሲል ተማሪ አዲሱ ለኢዜአ ተናግሯል።
ታዳጊው ከታህሳስ 7/2013ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት የተሰጠውን የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና በብቃት ውስዶ ዛሬ ረፋዱ ላይ ማጠናቀቁን ፈታኝ መምህሩ ተናግረዋል።
ተማሪ አዲሱ በቀጣይ ቀናት ሶስተኛ የቀዶ ህክምና ተደርጎለት በጤናው ላይ መሻሻል ካሳየ ከሆስፒታል እንደሚወጣ ተገልጿል። ጥቃት ያደረሰበት ተጠርጣሪም በቁጥጥር ስር መዋሉን ፓሊስ ገልጿል።