ከህዳር 7/2013ዓ.ም ጀምሮ ከ8ኛ እና 12ኛ ክፍል አዲስ ተማሪዎች ወጪ ያሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንደሚመለሱ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ገልጿል፡፡
የኮቪድ-19 ፕሮቶኮልን በተከተለ መልኩ ትምህርት ለማስጀመር ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የቢሮው ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የአምና 8ኛ እና 12ኛ ክፍል የነበሩ ተማሪዎች ከጥቅምት 18 ጀምሮ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አዲስ የ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ግን አሁን ላይ እንደማይስተናገዱም ተገልጿል።
በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በክልሉ 11 ነጥብ 2 ሚሊየን ተማሪዎችን ለመመዝገብ የታቀደ ቢሆንም፤ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ያህል ተማሪዎች አለመመዝገባቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል።
ኮቪድን-19ን ከመከላከል አንፃር ትምህርት ሚኒስቴር ለተማሪዎች 20 ሚሊየን ማስክ ለመስጠት ቃል የገባ ቢሆንም፣ ማስክ የሚያመርቱ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በፍጥነት ማምረት ባለመቻላቸው እስካሁን የደረሰው 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብቻ ነው ብለዋል።
ተማሪዎችን ያለ ማስክ ትምህርት ለማስጀመር ስለማይቻልም ወላጆች ልጆቻቸውን ማስክ፣ ሳኒታይዘር እንዲሁም ውሃ እንዲያሲዙም ኃላፊው ጠይቀዋል። (WaltaTv)