ትምህርት ሚኒስቴር ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ሚነስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ አስታወቁ።
ጥር 25/2015ዓም (ትምህርት ሚኒስቴር ) ሚኒስትሩ በጦርነት የወደሙና በልዪ ሁኔታ የሚገነቡ 71 ትምህርት ቤቶችን ስራ በይፋ አስጀምረዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በ71 ትምህርት ቤቶች ይፋዊ ስራ ማስጀመሪያ መርሀግብር ላይ እንደገለጹት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ትምህርት ቤቶች በተሻለ ዲዛይን የሚጠበቅባቸውን መሠረተ ልማት አሟልተው ይገነባሉ።
ምቹና የተሻሉ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ለትምህርት ጥራት ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ትምህርት ቤቶቹ በዚህ ዓመት ተገንብተው እስከ መጪው መስከረም ወር ድረስ ለአገልግሎት እንደሚበቁ ተናግረዋል።
ከ71 ትምህርት ቤቶች መካከል 50ዎቹ በዓለም ባንክ ድጋፍና ትብብር 16ቱ በሰዎች ለሰዎች ድርጅት እንዲሁም 5ቱ በዲያስፖራ ትረስት ፈንድ እንደሚገነቡ አመልክተዋል።
በመሆኑም የስራ ተቋራጮችና አማካሪዎች የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ ገንዘብና የጥራት ደረጃ ተገንብተው ለአገልግሎት እንዲበቁ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የትምህርት ፕሮግራሞችና ጥራት መሻሻል መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዩሐንስ ወጋሶ በበኩላቸው በጦርነት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን በተሻለ መንገድ ለመገንባት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ፣ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በጦርነት የወደሙ ትምህርት ቤቶች የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ግንባታቸው በዚህ ዓመት እንደሚጀመር ጠቁመዋል።
በመርሀግብሩ ላይ የተገኙ የስራ ተቋራጮች በበኩላቸው ግንባታዎቹ በታቀደላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታዎች ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌና ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ ፣ የሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት ሀገር አቀፍ ተጠሪ አቶ ይልማ ታዬ ፣ ኮንትራክተሮች ፣ የግንባታ አማካሪዎች ፣ የሚመለከታቸዉ ክፍሎች ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡