የ2013 የትምህርት ዘመን አንደኛ ዓመት ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲ መግቢያን በተመለከተ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
መንግስት ለትምህርት በሰጠው ልዩ ትኩረት ከአጠቃላይ ህዝባችን ከሩብ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ዜጎች በተለያየ ደረጃ በትምህርት ላይ ይገኛሉ፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ በሌሎች አገራት እምብዛም ባልተለመደ መልኩ መንግስት በየዓመቱ ቁጥራቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በነፃ ሊባል በሚችል ወጪ መጋራት በማስተማር ላይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ግማሽ ሚሊዮን ለሚደርሱ የመደበኛ ተማሪዎች በመንግስት የሚሸፈነው ዓመታዊ ወጪ በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠር እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ሪፎርም በጀመርንባቸው ያለፉት ሶስት ዓመታት የትምህርት ጥራትና ተገቢነት ቅድሚያ የርብርብ ማዕከላችን በማድረግ የተለያዩ የሪፎርም እርምጃዎች በመተግበር ላይ እንገኛለን፡፡
በዚሁ መሰረት የአንድ ዓመት የፍሬሽማን ፕሮግራም መጀመሩ፣ ዩኒቨርስቲዎችን በትኩረትና በተልዕኮ የመለየት፣ የፕሮግራምና ሥርዓተ ትምህርቶች ግምገማና ክለሳ ማካሄድ፣ የመምህራንና አሰልጠኞች ልማት ማጠናከር፣ የተቋማት አመራርና አሰራር ሪፎርም ትግበራ ማካሄድ እና የመሰረተ ልማት ማሟላትና የትምህርትና ስልጠና ጥራት ማሳደግ ፤ የመረጃ ሥራዎች አያያዝ አስተዳደር ማዘመን ፤ የትምህርት ፕሮግራሞች እና የተቋማት ብቃት ማረጋገጫ አስራር ስርዓት የማዘመን ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡
ካለፈው ዓመት ጀምሮ ወደ ትግበራ የገባው የፍሬሽ ማን ፕሮግራም የተማሪዎችን ቆይታ በትንሹ ወደ አራት ዓመት ያሳደገ ሲሆን ተማሪዎች በመጀመሪያው ዓመት የተለያዩ ክህሎቶችን፤ መሰረታዊ እውቀቶችንና እንዲጨብጡ የሚስችሉ ስብዕና ግንባታ ላይ ይዘት ያላቸው የትምህርት አይነቶችን የሚከታተሉባቸው ይሆናል፡፡ በያዝነው ዓመት የሚገቡ ተማሪዎች የመጀመሪያውን ዓመት ፍሬሽማን ፕሮግራም ካጠናቀቁ በኋላ ወደሚመርጧቸው ትምህርት ፕሮግራሞች ገብተው ለመከታተል የሚያስችላቸውን የእውቀትና ክህሎት ምዘና ፈተና በአገር አቀፍ ደረጃ ተዘጋጅቶ በየዩኒቨርስቲዎቻቸው የሚወስዱ ይሆናል፡፡ በፍሬሽማን ፕሮግራም ያስመዘገቡት ዉጤት እና በሃገር አቀፍ የሚሰጠውን የፈተና ዉጤት መሰረት በማድረግ በውጤታቸውና በምርጫቸው ተቋማቱ ወደ ፕሮግራሞች ቅበላ ያደርጋሉ፡፡
በዚህ ሂደት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዝቅተኛውን የመግቢያ መስፈርት የሚወስን ሲሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን የማሰልጠን፣ የማብቃት፣ የማዘጋጀትና አስፈላጊውን ክህሎት፣እውቀት እና ስብእና ግንባታ በተደራጀና በተሟላ ግብዓት የማስጨበጥ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ መምህራንም ያላቸውን ጊዜ በአግባቡ በመጠቀምና ከተቋማቸውና ተማሪዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት በመፍጠር ተማሪዎቻቸው አስፈላጊውን ክህሎትና፣ እውቀትና የተሻለ ስብዕና ይዘው እንዲገኙ የማብቃት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ተማሪዎችም በበኩላቸው ጊዜ ውድና ተመልሶ የማይገኝ መሆኑን በመገንዘብ ያላቸውን ቆይታ በአግባቡ ትምህርት ላይ ትኩረት በማድረግ፣ ካልተገቡ ነገሮች ራሳቸውን በማቀብ አስፈላጊውን እውቀት፣ክህሎት እና የተሻለ ስብዕና ይዘው የተሻሉ ሆነው ለመገኘት ቀን ከለሊት የመስራት ግዴታና የዜግነት ኃላፊነት አለባቸው፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በቀጣይ ዓመታት ለትምህርትና ሥልጠና ጥራትና ተገቢነት እንዲሁም ልህቀት መረጋገጥ ተጨማሪ እርምጃዎች በሴክተርና በተቋማት እንዲተገበሩ እየሰራ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችን ተቋማዊ ነፃነት የማረጋገጥና ከዚሁ ጋር የሚጣጣም የተማሪዎች ቅበላ ሥርዓት መዘርጋት ቁልፍ ተግባር ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ብዙ መስተጓጎል ያጋጠመበትን የ2012 / 2013 የትምህርት ዘመን በልዩ ሁኔታ ማስተናገድ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የተለያዩ ስልቶችን በመቀየስ ተግባራዊ አድርጓል፡፡
በቀጣይ የትምህርት ጊዚያት የቅበላ ስራውን ውጤታማ ለማድረግ በዋናነት የሁሉንም ፕሮግራሞች የስራ ገበያ ውጤታማነት የዳሰሳ ጥናት በሀገር ደረጃ የሚደረግ ይሆናል፡፡ በመሆኑም የጥናቱን ውጤት መሰረት አድርጎ ለሀገራችን ልማት አስተዋጽኦ በሚያደርግ መልኩና የተመራቂዎችን የስራ ዕድል በሚያሰፋ መልኩ የተማሪዎች ቅበላ በየተቋማቱ የሚከናወን ይሆናል፡፡ የትምህርት ፕሮግራሞቻችንም የስራ ገበያን ባማከለ መልኩ እንዲሆኑ ተከታታይነት ባለው መልኩ የመፈተሸ ስራው የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ይህን ተግባር በተገቢው መልኩ ለመፈጸም የምዘና ማዕከላትን የማደራጀት በድጅታል ስርአት ታገዙ የማድረግና የማጠናከር ስራ ይሰራል፡፡ይህንን መሰረት ተደርጎ የተማሪዎች ምዘና ስርአት ግልጽ ሆኖ የሚተገበር ይሆናል፡፡
መጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር