ትምህርት ሚኒስቴር አዲሱን የአጠቃላይ ትምህርት ስርዓተ-ትምህርት ለማሻሻልና የመጨረሻ ቅርጽ አስይዞ ወደ ተግባር ለማስገባት አውደ ጥናት እያካሄደ ነው።
አውደ ጥናቱ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት አምስት ዩኒቨርሲቲዎችን በማሳተፍ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
መድረኩ ቀደም ሲል የተሰበሰቡ ግብዓቶችን መሰረት በማድረግ የአዲሱ የአጠቃላይ ትምህርት ስርዓተ-ትምህርት ለማሻሻልና የመጨረሻ ቅርጽ አስይዞ ወደ ተግባር ለማስገባት ያለመ ነው።
የትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ተወካይ ዳይሬክተር ወ/ሮ ዛፏ አብርሃ የስርዓተ-ትምህርት ማሻሻያው ባለፉት ጊዜያት ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ 12ኛ ክፍል የነበሩትን የስርዓተ ትምህርት ችግሮችን ሊቀርፍ በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሥርዓተ ትምህርቱ ዝግጅት የይዘት ፍሰቱ፣ ተፈላጊ የመማር ብቃት መለኪያና ሰነዶች በሀገር ውስጥ እና በአለም አቀፍ ያሉ የብቃት ማረጋጋጫ ተቋማት ተሞክሮዎችን በመውሰድ የተገመገመ መሆኑን ጠቁመዋል። ፡፡
ዝግጅቱ በሂደት ላይ ያለው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ተማሪ በመልካም ስነ ምግባር የታነፀ እንዲሆን የግብረገብ ትምህርትን ያካተተ ፣ ወቅቱን የጠበቀ እና ለተማረ ዜጋ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው ተብሏል።
በሥርዓተ ትምህርቱ አዘገጃጀት ሂደት በቋንቋ፣ በሂሳብ፣ በሳይንስና በማህበራዊ ትምህርት ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከአምስቱ ከፍተኛ ትምህርት የልዕቀት ማዕከላት የተውጣጡ የዘርፉ ምዑራን፣ ባለሙያዎችና የሲቭል ማህበራት ተሳታፊ ሆኖዋል።
ለአዲሱ ሥርዓተ ትምህርቱ ማሻሻያ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ከተጠናቀቀ በኋላ ለትግበራ ወደ ክልሎች ይላካል ተብሏል።