በትግራይ ክልል በሚገኙ 4ቱም ዩኒቨርሲቲዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንደሚሰጥ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር አስቴር ይትባረክ ገልፀዋል።
ኢ/ር አስቴር እንደገለፁት ፤ በፀጥታ ስጋት ምክንያት ሁሉም የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች በትግራይ ውስጥ በሚገኙ መቐለ ፣ ዓዲግራት ፣ ራያ እና ኣክሱም ዩኒቨርሲቲዎች ይፈተናሉ፡፡
ከፈተናው በፊት ለተፈታኞቹ ለፈተና ዝግጁነት የሚረዳ ስልጠና በዩኒቨርሲቲዎቹ እንደሚሰጥ የጠቆሙት ኢንጅነር አስቴር፤ የመፈተን ምርጫው የተማሪዎች እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
አብዛኛው ተማሪዎች ከ18 ዓመት በላይ ስለሆኑ በፍላጎታቸውና በወላጆቻቸው ፍላጎት ፈተናው መውሰድ እንደሚችሉ የገለፁት ምክትል ኃላፊዋ ፤ ፈተናውን እወስዳለሁ የሚል ተማሪ እንደሚፈተንና አልፈተንም የሚል ደግሞ ለቀጣይ ዓመት እንደሚፈተን አስታውቀዋል፡፡
መምህራን የካቲት 8 ጀምሮ ስራ እንዲጀምሩ መመሪያ መውረዱን ያስታወሱት ኃላፊዋ፤ ከጸጥታና በትምህርት መሰረተ ልማቶች ላይ ከደረሰው ውድመት ጋር በተያያዘ ሁኔታዎች ፈታኝ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
የአስተማሪዎች ደመወዝ ሌላው ችግር መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊዋ ፤ በተለይ የግል ትምህርት ቤቶች በችግር ውስጥ እንደሚገኙና መንግስት ይሁን ሌሎች ተቋማት ትኩረት ሰጥተው እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ምንጭ፦ ወጋሕታ ጋዜጣ