በኢትዮጵያ ከመንግስት እና ከግል ትምህርት ተቋማት የተመረቁ ተማሪዎችን ማስረጃ ትክክለኛነት ማረጋገጥ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴ ተናገሩ።
ዶ/ር አንዱዓለም ይህን ያሳወቁት ከፋና ብሮድካስቲንግ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው።
አሰራሩ ተቋማት እና ግለሰቦች ሰራተኞችን ለመቅጠር በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እንዳይታለሉ ይረዳል ብለዋል ዶ/ር አንዱዓለም።
በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ሀሰተኛ እና የተሳሳተ የትምህርት ማስረጃን ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ የሚጠይቀው ሂደት ረጅም በመሆኑ አድካሚ ሆኖ ቆይቷል።
አሁን ግን ከተለያዩ ተቋማት ጋር ጥምረት በመፍጠር በቴክኖሎጂ የተደገፈ የተደራጀ መረጃ ለሚፈልግ አካል ለመሰጠት ስራዎች መጠናቀቃቸውን አሰታውቀዋል።
ስራውን ለማስጀመር የኤጀንሲው ሰራተኞች በቂ ስልጠና መውሰዳቸውን ገልፀዋል፡፡
የህግ ተጠያቂነት እንዲኖረውም ከጠቅላይ አቃቢ ህግ ፣ ከፌዴራል ፖሊስ ፣ ከፀረ ሙስና ኮሚሽን ፣ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ከቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር እንዲሁም ከ ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት ኤጀነሲ ጋር በጋራ እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ስራዎቹ ተጠናቀው በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆኑም ገልፀዋል፡፡
ምንጭ፦ ኤፍ ቢ ሲ